ምዕራፍ 6።

1፤2፤ አንተ ልጅህም የልጅ ልጅህም በዕድሜአችሁ ሁሉ ልትወርሱአት በምትገቡባት ምድር ታደርጉአት ዘንድ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ፈርተህ እኔ ለአንተ ያዘዝሁትን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ ዕድሜህም ይረዝም ዘንድ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንዳስተምራችሁ ያዘዛት ትእዛዝና ሥርዓት ፍርድም ይህች ናት።

3፤ እንግዲህ፥ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ መልካምም እንዲሆንልህ፥ የአባቶችህም አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወተትና ማር በምታፈስሰው ምድር እጅግ እንድትበዛ፥ ታደርጋት ዘንድ ጠብቅ።

4፤ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤

5፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ።

6፤ እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ።

7፤ ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው።

8፤ በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ።

9፤ በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።

10፤ አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተ ሊሰጣት ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ባገባህ ጊዜ፤ ያልሠራሃቸውንም ታላቅና መልካም ከተሞች፥

11፤ ያልሞላሃቸውንም ሀብትን የሞሉ ቤቶች፥ ያልማስሃቸውንም የተማሱ ጕድጓዶች፥ ያልተከልሃቸውንም ወይንና ወይራ በሰጠህ ጊዜ፥ በበላህና በጠገብህም ጊዜ፤

12፤ በዚያን ጊዜ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ።

13፤ አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፤ በስሙም ማል።

14፤15፤ በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና የአምላክህ የእግዚአብሔር ቍጣ እንዳይነድድብህ ከምድርም ፊት እንዳያጠፋህ፥ በዙሪያችሁ ያሉት አሕዛብ የሚያመልኩአቸውን ሌሎችን አማልክት አትከተሉ።

16፤ በማሳህ እንደ ፈተናችሁት አምላካችሁን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት።

17፤ ለእናንተ ያዘዘውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ምስክሩንም ሥርዓቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ።

18፤19፤ መልካምም ይሆንልህ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርስዋን ትወርስ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ ያወጣልህ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ፊት ቅኑንና መልካሙን አድርግ።

20፤ በኋለኛው ዘመንም ልጅህ። አምላካችን እግዚአብሔር ያዘዛችሁ ምስክርና ሥርዓት ፍርድስ ምንድር ነው? ብሎ በጠየቀህ ጊዜ፥

21፤ አንተ ልጅህን በለው። በግብፅ የፈርዖን ባሪያዎች ነበርን፤ እግዚአብሔርም በጽኑ እጅ ከግብፅ አወጣን፤

22፤ እግዚአብሔርም ከግብፅና በፈርዖን በቤቱም ሁሉ ላይ እኛ እያየን ታላቅና ክፉ ምልክት ተአምራትም አደረገ።

23፤ ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር አግብቶ እርስዋን ይሰጠን ዘንድ ከዚያ አወጣን።

24፤ እንደ ዛሬም በሕይወት እንዲያኖረን፥ ሁልጊዜም መልካም እንዲሆንልን፥ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፈራ ዘንድ፥ ይህችንም ሥርዓት ሁሉ እናደርግ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘን።

25፤ እርሱም እንዳዘዘን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት እናደርጋት ዘንድ ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብንጠብቅ ለእኛ ጽድቅ ይሆንልናል።