ምዕራፍ 8።

1፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ እነሆም፥ የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነበረ።

2፤ እርሱም። አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነው አልሁት። እግዚአብሔርም አለኝ። ፍጻሜ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መጥቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም።

3፤ የመቅደሱ ዝማሬ በዚያ ቀን ዋይታ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የሰዎችም ሬሳ ይበዛል፥ በስፍራውም ሁሉ በዝምታ ይጣላል።

4፤ ችጋረኛውን የምትውጡ፥ የአገሩንም ድሀ የምታጠፉ እናንተ ሆይ።

5፤ እህልን እንሸጥ ዘንድ መባቻው መቼ ያልፋል? የኢፍ መስፈሪያውንም እያሳነስን፥ ሰቅሉንም እያበዛን፥ በሐሰተኛም ሚዛን እያታለልን፥

6፤ ድሀውን በብር ችጋረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ እንገዛ ዘንድ፥ የስንዴውን ግርድ እንሸጥ ዘንድ ስንዴውን እንድንሸምት ሰንበት መቼ ያልፋል? የምትሉ እናንተ ሆይ፥ ይህን ስሙ።

7፤ እግዚአብሔር በያዕቆብ ክብር እንዲህ ብሎ ምሎአል። ሥራቸውን ሁሉ ለዘላለም ምንም አልረሳም።

8፤ በውኑ ምድሪቱ ስለዚህ ነገር አትናወጥምን? በእርስዋም የሚኖር ሁሉ አያለቅስምን? ሙላዋም እንደ ወንዙ ትነሣለች፤ እንደ ግብጽም ወንዝ ትነሣለች ደግሞም ትወርዳለች።

9፤ በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በብርሃንም ቀን ምድሩን አጨልማለሁ።

10፤ ዓመት በዓላችሁንም ወደ ልቅሶ፥ ዝማሬአችሁንም ወደ ዋይታ እለውጣለሁ፤ ማቅንም በወገብ ሁሉ፥ ራስ መንጨትንም በሁሉ ላይ አመጣለሁ፤ እንደ አንድያ ልጅም ልቅሶ፥ ፍጻሜውንም እንደ መራራ ቀን አደርገዋለሁ።

11፤ እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም።

12፤ ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፥ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ለመሻት ይርዋርዋጣሉ፥ አያገኙትምም።

13፤ በዚያ ቀን መልካካሞች ደናግል ጐበዛዝትም በጥም ይዝላሉ።

14፤ በሰማርያ ኃጢአት የሚምሉና። ዳን ሆይ፥ ሕያው አምላክህን! ደግሞ። ሕያው የቤርሳቤህን መንገድ! ብለው የሚሉ፥ እነርሱ ይወድቃሉ፥ ደግሞም አይነሡም።