ምዕራፍ 2።

1፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የኤዶምያስን ንጉሥ አጥንት አመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሎታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የሞዓብ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።

2፤ በሞዓብ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የቂርዮትንም አዳራሾች ትበላለች፤ ሞዓብም በውካታና በጩኸት በመለከትም ድምፅ ይሞታል፤

3፤ ፈራጅንም ከመካከልዋ አጠፋለሁ፥ ከእርሱም ጋር አለቆችዋን ሁሉ እገድላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

4፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእግዚአብሔርን ሕግ ጥለዋልና፥ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፥ አባቶቻቸውም የተከተሉት ሐሰታቸው አስቶአቸዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የይሁዳ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።

5፤ በይሁዳ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም አዳራሾች ትበላለች።

6፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጻድቁን ስለ ብር፥ ችጋረኛውንም ስለ አንድ ጥንድ ጫማ ሽጠውታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የእስራኤል ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።

7፤ የድሆችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፥ የትሑታንንም መንገድ ያጣምማሉ፤ ቅዱሱንም ስሜን ያረክሱ ዘንድ አባትና ልጁ ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፤

8፤ በመሠዊያውም ሁሉ አጠገብ ለመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ ይተኛሉ፤ በአምላካቸውም ቤት ውስጥ በካሣ የተወሰደውን ወይን ጠጅ ይጠጣሉ።

9፤ እኔ ግን ቁመቱ እንደ ዝግባ ቁመት፥ ብርታቱም እንደ ኮምበል ዛፍ የነበረውን አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁ፤ ፍሬውንም ከላዩ፥ ሥሩንም ከታቹ አጠፋሁ።

10፤ የአሞራዊውንም ምድር ትወርሱ ዘንድ ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፥ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ።

11፤ ከወንድ ልጆቻችሁም ነቢያትን፥ ከጐበዛዝቶቻችሁም ናዝራውያንን አስነሣሁ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ይህ እንደዚህ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር።

12፤ እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤ ነቢያቱንም። ትንቢትን አትናገሩ ብላችሁ አዘዛችኋቸው።

13፤ እነሆ፥ ነዶ የተሞላች ሰረገላ እንደምትደቀድቅ እንዲሁ እደቀድቃችኋለሁ።

14፤ ከርዋጪም ሽሽት ይጠፋል፥ ብርቱውም በብርታቱ አይበረታም፥ ኃያሉም ነፍሱን አያድንም፤

15፤ ቀስተኛውም አይቆምም፥ ፈጣኑም አይድንም፥ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም፤

16፤ በኃያላኑም መካከል ልበ ሙሉው በዚያ ቀን ዕራቁቱን ሆኖ ይሸሻል፥ ይላል እግዚአብሔር።