ምዕራፍ 24።

1፤ በእርሱም ዘመን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነዖር ወጣ፥ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ተገዛለት፤ ከዚያም በኋላ ዘወር አለና ዐመፀበት።

2፤ እግዚአብሔርም የከለዳውያንንና የሶርያውያንን የሞዓባውያንንም የአሞንንም ልጆች አደጋ ጣዮች ሰደደበት፤ በባሪያዎቹ በነቢያት እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ያጠፉት ዘንድ በይሁዳ ላይ ሰደዳቸው።

3፤ ምናሴ ስላደረገው ኃጢአት ሁሉ ስላፈሰሰውም ንጹሕ ደም፥ ኢየሩሳሌምንም በንጹሕ ደም ስለሞላ ከፊቱ ያስወግዳቸው ዘንድ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ትእዛዝ በይሁዳ ላይ ሆነ፤

4፤ እግዚአብሔርም ይራራ ዘንድ አልወደደም።

5፤ የቀረውም የኢዮአቄም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

6፤ ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዮአኪን፤ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

7፤ የባቢሎንም ንጉሥ ለግብጽ ንጉሥ የነበረውን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ወስዶ ነበርና የግብጽ ንጉሥ ከዚያ ወዲያ ከአገሩ አልወጣም።

8፤ ዮአኪን መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስምንት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ፤ እናቱም ኔስታ ትባል ነበር፤ እርስዋም የኢየሩሳሌም ሰው የኤልናታን ልጅ ነበረች።

9፤ አባቱም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

10፤ በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነዖር ባሪያዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፥ ከተማይቱም ተከበበች።

11፤ ባሪያዎቹም በከበቡአት ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናብከደነዖር ወደ ከተማይቱ ወጣ።

12፤ የይሁዳም ንጉሥ ዮአኮንና እናቱ፥ ባርያዎቹም፥ አለቆቹም፥ ጃንደረቦቹም ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወጡ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ያዘው።

13፤ የእግዚአብሔርም ቤት መዛግብትን ሁሉ የንጉሡም ቤት መዛግብትን ከዚያ አወጣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር መቅደስ የሠራውን የወርቁን ዕቃ ሁሉ ሰባበረ።

14፤ ኢየሩሳሌምንም ሁሉ፥ አለቆቹንም ሁሉ፥ ጽኑዓን ኃያላኑንም ሁሉ፥ ጠራቢዎቹንም ሁሉ፥ ብረት ሠራተኞቹን ሁሉ አሥር ሺህ ምርኮኞች አፈለሰ፤ ከድሆች ከአገሩ ሕዝብ በቀር ማንም አልቀረም።

15፤ ዮአኮንንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ፤ የንጉሡንም እናት፥ የንጉሡንም ሚስቶች፥ ጃንደረቦቹንም፥ የአገሩንም ታላላቆች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማረከ።

16፤ የባቢሎንም ንጉሥ ብርቱዎቹንና ሰልፍ የሚችሉትን ሁሉ፥ ኃያላኑን ሁሉ ሰባት ሺህ ያህል፥ ጠራቢዎችና ብረት ሠራተኞችም አንድ ሺህ፥ ወደ ባቢሎን ማረከ።

17፤ የባቢሎንም ንጉሥ የዮአኪንን አጎት ማታንያን በእርሱ ፋንታ አነገሠ፥ ስሙንም ሴዴቅያስ ብሎ ለወጠው።

18፤ ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም አሚጣል የተባለች የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።

19፤ ኢዮአቄምም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

20፤ ከፊቱ አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ቍጣ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆኖአልና፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።