ምዕራፍ 18።

1፤ እንዲህም ሆነ፤ በእስራኤል ንጉሥ በኤላ ልጅ በሆሴዕ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነገሠ።

2፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ነበረች።

3፤ እርሱም አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ።

4፤ በኮረብታም ያሉትን መስገጃዎች አስወገደ፥ ሐውልቶችንም ቀለጣጠመ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የእስራኤልም ልጆች እስከዚህ ዘመን ድረስ ያጥኑለት ነበርና ሙሴ የሠራውን የናሱን እባብ ሰባበረ፤ ስሙንም ነሑሽታን ብሎ ጠራው።

5፤ በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱም በኋላ ከእርሱም በፊት ከነበሩት ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ እርሱን የሚመስል አልነበረም።

6፤ ከእግዚአብሔርም ጋር ተጣበቀ፥ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፥ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዘውን ትእዛዛቱን ጠበቀ።

7፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፥ የሚሄድበትም መንገድ ተከናወነለት፤ በአሦርም ንጉሥ ላይ ዐመፀ፥ አልገበረለትም።

8፤ ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጋዛና እስከ ዳርቻዋ ድረስ፥ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ምሽጉ ከተማ ድረስ መታ።

9፤ በንጉሡ በሕዝቅያስ በአራተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በኤላ ልጅ በሆሴዕ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ወጣ፥ ከበባትም።

10፤ ከሦስት ዓመት በኋላም ወሰዳት፤ በሕዝቅያስ በስድስተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በሆሴዕ በዘጠኝኛው ዓመት፥ ሰማርያ ተያዘች።

11፤ የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ወደ አሦር አፈለሰ፥ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው፤

12፤ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙምና፥ ቃል ኪዳኑንም አፍርሰዋልና፥ የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አልሰሙምና፥ አላደረጉምና።

13፤ በንጉሡም በሕዝቅያስ በአሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጣ፥ ወሰዳቸውም።

14፤ የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ። በድያለሁ፥ ከእኔ ተመለስ፤ የምትጭንብኝን ሁሉ እሸከማለሁ ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ለኪሶ ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ ጫነበት።

15፤ ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የተገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው።

16፤ በዚያን ጊዜም ሕዝቅያስ ከእግዚአብሔር መቅደስ ደጆችና የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከለበጣቸው መቃኖች ወርቁን ቈረጠ፥ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠው።

17፤ የአሦርም ንጉሥ ተርታንንና ራፌስን ራፋስቂስንም ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ። ወጥተውም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ በመጡም ጊዜ በአጣቢው እርሻ መንገድ ባለችው በላይኛይቱ ኩሬ መስኖ አጠገብ ቆሙ።

18፤ ንጉሡንም ጠሩ፤ የቤቱም አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ወጡ።

19፤ ራፋስቂስም አላቸው። ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ይህ የምትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው?

20፤ የከንፈር ቃል ለሰልፍ ምክርና ኃይል እንደሚሆን ትናገራለህ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው?

21፤ እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብጽ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል ያቈስለውማል፤ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው።

22፤ እናንተም። በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትሉኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን። በኢየሩሳሌም ባለው በዚህ መሠዊያ ፊት ሰገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያውቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን?

23፤ አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፥ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ።

24፤ ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሰኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱ አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል?

25፤ አሁን በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን ስፍራ አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር። ወደዚች አገር ወጥተህ አጥፋት አለኝ።

26፤ የኬልቅያስም ልጅ ኤልያቄም ሳምናስም ዮአስም ራፋስቂስን። እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን አሉት።

27፤ ራፋስቂስ ግን። ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን? አላቸው።

28፤ ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኽ። የታላቁን የአሦር ንጉሥ ቃል ስሙ፤ ንጉሡ እንዲህ ይላል።

29፤ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤

30፤ ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል፥ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።

31፤ ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ውጡ፥ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤

32፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን፥ ወይራና ማር ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ በሕይወት እንድትኖሩ እንዳትሞቱም ነው። ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ ቢያታልላችሁ አትስሙት።

33፤ በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን?

34፤ የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይምና የሄና የዒዋም አማልክት ወዴት አሉ?

35፤ ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከአገሮቹ አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?

36፤ ሕዝቡም ዝም አሉ፥ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና።

37፤ የቤቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፥ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።