ምዕራፍ 29።

1፤ ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን ሁሉ ወደ አፌቅ ሰበሰቡ፤ እስራኤላውያንም በኢይዝራኤል ባለው ውኃ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ።

2፤ የፍልስጥኤማውያንም አለቆች በመቶ በመቶ በሺህ በሺህ እየሆኑ ያልፉ ነበር፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከአንኩስ ጋር በኋለኛው ጭፍራ በኩል ያልፉ ነበር።

3፤ የፍልስጥኤማውያንም አለቆች። እነዚህ ዕብራውያን በዚህ ምን ያደርጋሉ? አሉ፤ አንኩስም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች። ይህ የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል ባሪያ ዳዊት አይደለምን? እርሱም በእነዚህ ቀኖች በእነዚህ ዓመታት ከእኔ ጋር ነበረ፥ ወደ እኔም ከተጠጋበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ምንም አላገኘሁበትም አላቸው።

4፤ የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን ተቆጥተው። ይህ ሰው ባስቀመጥኸው ስፍራ ይቀመጥ ዘንድ ይመለስ፤ በሰልፉ ውስጥ ጠላት እንዳይሆነን ከእኛ ጋር ወደ ሰልፍ አይውረድ፤ ከጌታው ጋር በምን ይታረቃል? የእነዚህን ሰዎች ራስ በመቍረጥ አይደለምን?

5፤ ወይስ ሴቶች። ሳኦል ሺህ ገደለ፥ ዳዊት እልፍ ገደለ ብለው በዘፈን የዘመሩለት ይህ ዳዊት አይደለምን? አሉት።

6፤ አንኩስም ዳዊትን ጠርቶ። ሕያው እግዚአብሔርን! አንተ ቅን ነህ፥ ከእኔም ጋር በጭፍራው በኩል መውጣትህና መግባትህ በፊቴ መልካም ነው፤ ወደ እኔም ከመጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አንዳች ክፋት አላገኘሁብህም፤ ነገር ግን በአለቆች ዘንድ አልተወደድህም።

7፤ አሁንም ተመልሰህ በደኅና ሂድ፥ በፍልስጥኤማውያንም አለቆች ዓይን ክፋት አታድርግ አለው።

8፤ ዳዊትም አንኩስን። ምን አድርጌአለሁ? ሄጄስ ከጌታዬ ከንጉሡ ጠላቶች ጋር እንዳልዋጋ፥ በፊትህ ከተቀመጥሁ ጀምሬ እስከ ዛሬ ድረስ በእኔ በባሪያህ ምን አግኝተህብኛል? አለው።

9፤ አንኩስም መልሶ ዳዊትን። እንደ አምላክ መልእክተኛ በዓይኔ ፊት መልካም እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ነገር ግን የፍልስጥኤማውያን አለቆች። ከእኛ ጋር ወደ ሰልፍ አይወጣም አሉ።

10፤ አሁንም አንተ ከአንተም ጋር የመጡ የጌታህ ባሪያዎች ማልዳችሁ ተነሡ፤ ሲነጋም ተነሥታችሁ ሂዱ አለው።

11፤ ዳዊትና ሰዎቹም ማልደው ይሄዱ ዘንድ፥ ወደ ፍልስጥኤማውያንም አገር ይመለሱ ዘንድ ተነሡ። ፍልስጥኤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ወጡ።