ምዕራፍ 12።

1፤ ሳሙኤልም እስራኤልን ሁሉ አለ። የነገራችሁኝን ሁሉ ሰምቼ አንግሼላችኋለሁ።

2፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ንጉሡ በፊታችሁ ይሄዳል፤ እኔም አርጅቻለሁ ሸምግያለሁም፤ እነሆም፥ ልጆቼ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔም ከሕፃንነቴ ጀምሬ እስከ ዛሬ ድረስ በፊታችሁ ሄድሁ።

3፤ እነሆኝ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን ጋር እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? እኔም እመልስላችኋለሁ።

4፤ እነርሱም። አልሸነገልኸንም፥ ግፍም አላደረግህብንም፥ ከሰውም እጅ ምንም አልወሰድህም አሉ።

5፤ እርሱም። በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ እግዚአብሔርና እርሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክሮች ናቸው አላቸው፤ እነርሱም። ምስክር ነው አሉ።

6፤ ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ። ሙሴንና አሮንን ያላቀ፥ አባቶቻችሁንም ከግብጽ ምድር ያወጣ እግዚአብሔር ነው።

7፤ አሁንም እግዚአብሔር ለእናንተና ለአባቶቻችሁ ስላደረገው ጽድቅ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እምዋገታችሁ ዘንድ በዚህ ቁሙ።

8፤ ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ በገቡ ጊዜ ግብጻውያን አስጨነቁአቸው፤ አባቶቻችሁም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ላከ፥ አባቶቻችሁንም ከግብጽ አውጥተው በዚህ ቦታ አኖሩአቸው።

9፤ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ፥ ለአሶር ሠራዊትም አለቃ ለሲሣራ እጅ፥ ለፍልስጥኤማውያንም እጅ፥ ለሞዓብም ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጉ።

10፤ እነርሱም። እግዚአብሔርን ትተን በኣሊምንና አስታሮትን በማምለካችን በድለናል፤ አሁንም ከጠላቶቻችን እጅ አድነን፥ እናመልክህማለን ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።

11፤ እግዚአብሔርም ይሩበአልም፥ ባርቅንም፥ ዮፍታሔንም፥ ሳሙኤልንም ላከ፥ በዙሪያችሁም ካሉት ከጠላቶቻችሁ እጅ አዳናችሁ፤ ተዘልላችሁም ተቀመጣችሁ።

12፤ የአሞንም ልጆች ንጉሥ ናዖስ እንደ መጣባችሁ ባያችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ንጉሣችሁ ሳለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይንገሥልን አላችሁኝ።

13፤ አሁንም የመረጣችሁትንና የፈለጋችሁትን ንጉሥ እዩ፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ንጉሥ አደረገላችሁ።

14፤ እግዚአብሔርን ብትፈሩ ብታመልኩትም፥ ቃሉንም ብትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ባታምፁ፥ እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትከተሉ፥ መልካም ይሆንላችኋል።

15፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ብታምፁ፥ በእናንተና በንጉሣችሁ ላይ የእግዚአብሔር እጅ ትሆናለች።

16፤ አሁንም ቁሙ፥ እግዚአብሔርም በዓይናችሁ ፊት ወደሚያደርገው ወደዚህ ታላቅ ነገር ተመልከቱ።

17፤ የስንዴ መከር ዛሬ አይደለምን? ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፥ እርሱም ነጎድጓድና ዝናብ ይልካል፤ እናንተም ንጉሥ በመለመናችሁ በእግዚአብሔር ፊት ያደረጋችሁት ክፋት ታላቅ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ ታያላችሁም።

18፤ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም በዚያን ቀን ነጐድጓድና ዝናብ ላከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩአቸው።

19፤ ሕዝቡም ሁሉ ሳሙኤልን። ንጉሥ በመለመናችን በኃጢአታችን ሁሉ ላይ ይህን ክፋት ጨምረናልና እንዳንሞት ስለ ባሪያዎችህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት።

20፤ ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ። አትፍሩ፤ በእውነት ይህን ክፋት ሁሉ አደረጋችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ።

21፤ ምናምንቴ ነውና የማይረባንና የማያድን ከንቱን ነገር ለመከተል ፈቀቅ አትበሉ።

22፤ እግዚአብሔር ለእርሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ወድዶአልና እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሕዝቡን አይተውም።

23፤ ደግሞ መልካሙንና ቅኑን መንገድ አስተምራችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይን በመተው እግዚአብሔርን እበድል ዘንድ ይህ ከእኔ ይራቅ።

24፤ ብቻ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ያደረገላችሁንም ታላቅ ነገር አይታችኋልና በፍጹም ልባችሁ በእውነት አምልኩት።

25፤ ነገር ግን ክፉ ብትሠሩ እናንተም ንጉሣችሁም ትጠፋላችሁ።