ምዕራፍ 3።

1፤ ብላቴናውም ሳሙኤል በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር፤ በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ፤ ራእይም አይገለጥም ነበር።

2፤ በዚያም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ የዔሊ ዓይኖች ማየት እስኪሳናቸው ድረስ መፍዘዝ ጀምረው ነበር።

3፤ ዔሊም በስፍራው ተኝቶ ሳለ፥ የእግዚአብሔር መብራት ገና ሳይጠፋ፥ ሳሙኤልም የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ሳለ፥

4፤ እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፤ እርሱም። እነሆኝ አለ።

5፤ ወደ ዔሊም ሮጠ። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም። አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ አለው። ሄዶም ተኛ።

6፤ እግዚአብሔርም ደግሞ። ሳሙኤል ሆይ ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም። ልጄ ሆይ፥ አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ ብሎ መለሰ።

7፤ ሳሙኤል ግን ገና እግዚአብሔርን አላወቀም ነበር፥ የእግዚአብሔርም ቃል ገና አልተገለጠለትም ነበር።

8፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ ጠራው። እርሱም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና። እነሆኝ የጠራኸኝ አለ። ዔሊም እግዚአብሔር ብላቴናውን እንደ ጠራው አስተዋለ።

9፤ ዔሊም ሳሙኤልን። ሄደህ ተኛ ቢጠራህም። አቤቱ፥ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር በለው አለው። ሳሙኤልም ሄዶ በስፍራው ተኛ።

10፤ እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፥ እንደ ቀድሞውም። ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም። ባሪያህ ይሰማልና ተናገር አለው።

11፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። እነሆ፥ የሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገርን በእስራኤል አደርጋለሁ።

12፤ በዚያም ቀን በቤቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ በዔሊ አወርዳለሁ፤ እኔም ጀምሬ እፈጽምበታለሁ።

13፤ ልጆቹ የእርግማን ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና ስለ ኃጢአቱ በቤት ለዘላለም እንድፈርድ አስታውቄዋለሁ።

14፤ ስለዚህም የዔሊ ቤት ኃጢአት በመሥዋዕትና በቍርባን ለዘላለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ።

15፤ ሳሙኤልም እስኪነጋ ተኛ፥ ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ። ሳሙኤልም ራእዩን ለዔሊ መንገር ፈራ።

16፤ ዔሊም ሳሙኤልን ጠርቶ። ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥ አለ፤ እርሱም። እነሆኝ አለ።

17፤ እርሱም። እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድር ነው? ከእኔ አትሸሽግ፤ ከነገረህ ነገር ሁሉ የሸሸግኸኝ እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብህ፥ እንዲህም ይጨምርብህ አለው።

18፤ ሳሙኤልም ነገሩን ሁሉ ነገረው፥ አንዳችም አልሸሸገውም። ዔሊም። እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ።

19፤ ሳሙኤልም አደገ፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ከቃሉም አንዳች በምድር ላይ አይወድቀም ነበር።

20፤ እስራኤልም ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ነቢይ ይሆን ዘንድ የታመነ እንደ ሆነ አወቀ።

21፤ እግዚአብሔርም ደግሞ በሴሎ ተገለጠ፤ እግዚአብሔርም በእግዚአብሔር ቃል ለሳሙኤል በሴሎ ይገለጥ ነበር። የሳሙኤልም ቃል ለእስራኤል ሁሉ ደረሰ።