ምዕራፍ 16።

1፤ የእግዚአብሔርም ቃል በባኦስ ላይ እንዲህ ብሎ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ።

2፤ እኔ ከመሬት አስነሥቼ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌሃለሁ፤ አንተ ግን በኢዮርብዓም መንገድ ሄደሃል፥ በኃጢአታቸውም ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቤን እስራኤልን አስተሃቸዋል።

3፤ ስለዚህም፥ እነሆ፥ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ እጠርጋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርጋለሁ።

4፤ ከባኦስም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሚሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሚሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል።

5፤ የቀረውም የባኦስ ነገር፥ ሥራውና ጭከናውም፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

6፤ ባኦስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቴርሳም ተቀበረ፤ ልጁም ኤላ በፋንታው ነገሠ።

7፤ በእጁም ሥራ ያስቈጣው ዘንድ፥ እንደ ኢዮርብዓም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ስላደረገው ክፋት ሁሉ እርሱንም ስለ ገደለው፥ የእግዚአብሔር ቃል በባኦስና በቤቱ ላይ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ኢዩ መጣ።

8፤ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሀያ ስድስተኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ በቴርሳ ሁለት ዓመት ነገሠ።

9፤ የእኩሌቶቹም ሰረገሎች አለቃ ዘምሪ ተማማለበት፤ ኤላም በቴርሳ ነበረ፥ በቴርሳም በነበረው በቤት አሽከሮች አለቃ በኦሳ ቤት ይሰክር ነበር።

10፤ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሀያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ ገብቶ መታው ገደለውም፥ በፋንታውም ነገሠ።

11፤ ንጉሥም በሆነ ጊዜ፥ በዙፋኑም በተቀመጠ ጊዜ፥ የባኦስን ቤት ሁሉ መታ፤ ከዘመዶችና ከወዳጆች ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ አልቀረም።

12፤13፤ ባኦስና ልጁ ኤላ ስለ ሠሩት ኃጢአት ሁሉ፥ በምናምንቴም ሥራቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ስለ አሳቱበት ኃጢአት፥ በነቢዩ በኢዩ እጅ በባኦስ ላይ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዘምሪ የባኦስን ቤት ሁሉ እንዲሁ አጠፋ።

14፤ የቀረውም የኤላ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

15፤ በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሀያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሰባት ቀን ነገሠ። ሕዝቡም በፍልስጥኤም አገር የነበረው ገባቶንን ከብበው ነበር።

16፤ ከተማይቱንም ከብበው የነበሩ ሕዝብ ዘምሪ እንደ ዐመፀ፥ ንጉሡንም እንደ ገደለ ሰሙ፤ እስራኤልም ሁሉ በዚያ ቀን በሰፈሩ ውስጥ የሠራዊቱን አለቃ ዘንበሪን አነገሡ።

17፤ ዘንበሪም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከገባቶን ወጥተው ቴርሳን ከበቡ።

18፤ ዘምሪም ከተማይቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ገባ፥ የንጉሡንም ቤት በራሱ ላይ በእሳት አቃጠለ፤

19፤ ስላደረገውም ኃጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት ኃጢአት፥ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርጎአልና፥ በኢዮርብዓምም መንገድ ሄዶአልና ሞተ።

20፤ የቀረውም የዘምሪ ነገር፥ ያደረገውም ዐመፅ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

21፤ በዚያም ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ በሁለት ተከፈለ፤ የሕዝቡም እኩሌታ የጎናትን ልጅ ታምኒን ያነግሡት ዘንድ ተከተለው፤ እኩሌታውም ዘንበሪን ተከተለ።

22፤ ዘንበሪንም የተከተለ ሕዝብ የጎናትን ልጅ ታምኒን በተከተለ ሕዝብ ላይ በረታ፤ ታምኒም ሞተ፥ ዘንበሪም ነገሠ።

23፤ በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሠላሳ አንደኛው ዓመት ዘንበሪ በእስራኤል ላይ አሥራ ሁለት ዓመት ነገሠ። በቴርሳም ስድስት ዓመት ነገሠ።

24፤ ከሳምርም በሁለት መክሊት ብር የሰማርያን ተራራ ገዛ፤ በተራራውም ላይ ሠራ፥ የሠራውንም ከተማ በተራራው ባለቤት በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ጠራው።

25፤ ዘንበሪም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፥ ከእርሱም አስቀድሞ ከነበሩት ይልቅ እጅግ ከፋ።

26፤ በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሁሉ በምናምንቴም ነገራቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ባሳተበት ኃጢአት ሄደ።

27፤ የቀረውም ዘንበሪ ያደረገው ነገር፥ የሠራውም ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

28፤ ዘንበሪም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ተቀበረ፤ ልጁም አክዓብ በፋንታው ነገሠ።

29፤ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዘንበሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ የዘንበሪም ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ በሰማሪያ ሀያ ሁለት ዓመት ነገሠ።

30፤ የዘንበሪም ልጅ አክዓብ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

31፤ በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት መሄድ ታናሽ ነገር መሰለው፥ የሲዶናውያንንም ንጉሥ የኤትበኣልን ልጅ ኤልዛቤልን አገባ፥ ሄዶም በኣልን አመለከ ሰገደለትም።

32፤ በሰማርያም በሠራው በበኣል ቤት ውስጥ ለበኣል መሠዊያ አቆመ።

33፤ አክዓብም የማምለኪያ ዐፀድ ተከለ፤ አክዓብም ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያስቈጣውን ነገር አበዛ።

34፤ በእርሱም ዘመን የቤቴል ሰው አኪኤል ኢያሪኮን ሠራ፤ በነዌም ልጅ በኢያሱ እጅ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ በበኵር ልጅ በአቢሮን መሠረትዋን አደረገ፥ በታናሹ ልጁም በሠጉብ በሮችዋን አቆመ። a