ምዕራፍ 15።

1፤ ዳዊትም በከተማው ላይ ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔርም ታቦት ስፍራ አዘጋጀ፥ ድንኳንም ተከለለት።

2፤ በዚያን ጊዜም ዳዊት። የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከሙ ዘንድ፥ ለዘላለሙም ያገለግሉት ዘንድ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር ማንም የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከም ዘንድ አይገባውም አለ።

3፤ ዳዊትም ወዳዘጋጀለት ስፍራ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ እስራኤልን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ።

4፤ ዳዊትም የአሮንን ልጆችና ሌዋውያንን ሰበሰበ።

5፤ ከቀዓት ልጆች፤ አለቃው ኡርኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሀያ፤

6፤ ከሜራሪ ልጆች፤ አለቃው ዓሣያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ ሀያ፤

7፤ ከጌድሶን ልጆች፤ አለቃው ኢዮኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሠላሳ፤

8፤ ከኤሊጻፋን ልጆች፤ አለቃው ሸማያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ፤

9፤ ከኬብሮን ልጆች፤ አለቃው ኤሊኤል፥ ወንድሞቹም ሰማንያ፤

10፤ ከዑዝኤል ልጆች፤ አለቃው አሚናዳብ፥ ወንድሞቹም መቶ አሥራ ሁለት።

11፤ ዳዊትም ካህናቱን ሳዶቅንና አቢያታርን፥ ሌዋውያንንም ኡርኤልን፥ ዓሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሸማያን፥ ኤሊኤልን፥ አሚናዳብንም ጠርቶ።

12፤ እናንተ የሌዋውያን አባቶች ቤቶች አለቆች ናችሁ፤ ወዳዘጋጀሁለት ስፍራ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ታመጡ ዘንድ እናንተና ወንድሞቻችሁ ተቀደሱ።

13፤ ቀድሞም አልተሸከማችሁምና፥ እንደ ሥርዓቱም አልፈለግነውምና አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን ስብራት አደረገ አላቸው።

14፤ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጡ ዘንድ ካህናቱና ሌዋውያኑ ተቀደሱ።

15፤ ሙሴም እንዳዘዘው እንደ እግዚአብሔር ቃል የሌዋውያን ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎቹ ተሸከሙ።

16፤ ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን ይሾሙ ዘንድ ለሌዋውያን ኣለቆች ተናገረ።

17፤ ሌዋውያኑም የኢዮኤልን ልጅ ኤማንን፥ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፥ ከወንድሞቻቸውም ከሜራሪ ልጆች የቂሳን ልጅ ኤታንን፥

18፤ ከእነርሱም ጋር በሁለተኛው ተራ የሆኑትን ወንድሞቻቸውን ዘካርያስን፥ ቤንን፥ ያዝኤልን፥ ሰሚራሞትን፥ ይሒኤልን፥ ዑኒን፥ ኤልያብን፥ በናያስን፥ መዕሤያን፥ መቲትያን፥ ኤሊፍሌሁን፥ ሚቅንያን፥ በረኞችንም ዖቤድኤዶምንና ይዒኤልን አቆሙ።

19፤ መዘምራንም ኤማንና አሳፍ ኤታንም በናስ ጸናጽል ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር።

20፤ ዘካርያስ፥ ዓዝዔል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ዑኒ፥ ኤልያብ፥ መዕሤያ፥ በናያስ በመሰንቆ ምሥጢር ነገር ያዜሙ ነበር።

21፤ መቲትያ፥ ኤልፍሌሁ፥ ሚቅኒያ፥ ዖቤድኤዶም፥ ይዒኤል፥ ዓዛዝያ ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ ነበር።

22፤ የሌዋውያኑም አለቃ ክናንያ በዜማ ላይ ተሹሞ ነበር። ብልሃተኛ ነበረና ዜማ ያስተምራቸው ነበር።

23፤ በራክያና ሕልቃናም ለታቦቱ በረኞች ነበሩ።

24፤ ካህናቱም ሰበንያ፥ ኢዮሳፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዓማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያስ፥ አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦይ ፊት መለከት ይነፉ ነበር። ዖቤድኤዶምና ይሒያም ለታቦቱ በረኞች ነበሩ።

25፤ ዳዊትም፥ የእስራኤልም ሽማግሌዎች፥ የሻለቆችም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢዳራ ቤት በደስታ ያመጡ ዘንድ ሄዱ።

26፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያንን እግዚአብሔር በረዳቸው ጊዜ ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች ሰዉ።

27፤ ዳዊትም፥ ታቦቱንም የተሸከሙ ሌዋውያን ሁሉ፥ መዘምራኑም፥ የመዘምራኑም አለቃ ከናንያ የጥሩ በፍታ ቀሚስ ለብሰው ነበር፤ ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ነበረው።

28፤ እንዲሁ እስራኤል ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም በገናም እየመቱ፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ።

29፤ የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት ሲዘፍንና ሲጫወት አይታ በልቧ ናቀችው።